የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በድሬዳዋ ከተማ

የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በሓረሪ ክልል ሐረር ከተማ ተከናወነ፡፡
በ2012 የአርንጓዴ አሻራ ዘመቻን የብኢኮ ዋና መ/ቤት የተለያዩ ስራ ክፍሎች በተወጣጡ ሠራተኞች ሃምሌ 26 እና 27 በ2012 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ምስ/ዕዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ እንዲሁም በሐረር ከተማ በሓረሪ ባህል ማዕከል የተለያዩ የመንገድ ጌጥኛ ዛፎችና የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለዋል፡፡
የኮርፖሬት ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሞላልኝ ከሳቴብርሃን ኮርፖሬሽኑ ከክልሎች ጋር በመሆን የማህበራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን በመግለፅ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የሐረር ክልል መስተዳደር ላደረገላቸው መልካም መስተንግዶ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡ ያደኑ ትርፌሳ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኦፕሬሽን ዘርፍ አማካሪ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የጀመረውን የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡        
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ መ/ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈያት ሙስጠፋ ኮርፖሬሽናችን በበረሃዋ ንግስት ድሬ ከተማ ላይ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን በማከናወኑ ምስጋናቸውን በከተማ አስተዳደሩ ስም አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይም የሓረር ከተማ መዘጋጃ ቤት የፅዳትና ውበት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ የተደረገውን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዛፎችን በመትከል ብቻ መቆም እንደሌለበት በማውሳት በቀጣይም እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በ2012 የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን አስመልክቶ በተደረገው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በሁለቱ ከተሞች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡