የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ

ኢትዮጵያ  የምትቀየረው ግብርናው ሲቀየር ብቻ ነው …በስቶራችን በርካታ ክምችት አለን ጥሩ የገበያ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል.."

ሻ/ቃ ድሪባ ሁንዴ  

የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ  ስራ አስኪያጅ

 

ግብርና በኢትዮጵያ ምጣኔያዊ ሀብት ዉስጥ ከፍተኛውን  ድርሻ ይይዛል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆነው ህዝቧ መተዳደሪያና ለኢንዱስትሪዎቿም የጥሬ እቃ አቅርቦት ምንጭ ነው፡፡ ሀገሪቷ ለግብርና ምርቷ ተስማሚ የሆነ ለም መሬት ፣ የአየር ንብረትና ውሃ ተፈጥሮ ችራታለች፡፡ነገር ግን የምትከተለው የአስተራረስ ዘዴ እጅግ ኋላ ቀር በመሆኑ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡በዝናብና በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊና ለም መሬት ባለቤት ብትሆንም አልተጠቀመችበትም፡፡ አርሶ አደሮቿ ለዘመናት የተከተሉት በእንስሳት ጉልበት የሚደረግ አስተራረስ ሀገሪቷን ከድህነት ሊያወጣት አልቻለም፡፡ ካላት የቆዳ ስፋት አንፃር በጥቅም ላይ የዋለው  መሬት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይህን ሊለማ የሚችል የመሬት ሐብት ለማልማትና ከድህነት ለመውጣት ግብርናው  ለውጥ ያስፈልገዋል ::

 

ያለው የግብርና አመራረት ሂደት ቀጣይ ከሆነ ሀገሪቱ ያላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር  አሳሳቢ በመሆኑ እየጨመረ ካለው የህዝብ ብዛት አኳያ ራሳችንን የመመገብ አቅማችን ከባድ ፈተና ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ታዲያ  ይህን ህዝብ  ለመመገብ ሚካናይዝድ የሆነ የግብርና ቴክኖሎጂን መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ነው ምሁራን የሚጠቅሱት፡፡ የማረሻ ፣ የመዝሪያ እና የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ መለማመድና መጠቀም እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ::

አርሶ አደሩ በወቅቱ አርሶ፣ ዘርቶና አጭዶ  ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ብሎም ለገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች በማምረት ኑሮውን እንዲለውጥ ለማስቻል የግብርና ሚካናይዜሽን ተጠቃሚ መሆን ያሻዋል ፡፡ የግብርናዉ ዘርፍ ለማክሮ ኢኮኖሚዉ ዘርፍ ዕድገት የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ድርሻ እንዲያበረክት ከተፈለገ ዘርፉም በተሻሻሉ ዘመናዊ ግብዓቶች እንዲታገዝ ለማስቻል ዝናብን ብቻ በመጠበቅ ከሚከናወን እርሻ በመላቀቅ የመስኖ እርሻን ማስፋፋት ወሳኝ ነው፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን  ስርዓት/ሲስተም ማምረትና  ማሰራጨትን፣ ኦፕሬሽንን ጥገናን፣ እንክብካቤን ማስተዳደርን፣ የፋይናንስ ግኝትንና የአፈፃፀም ቢዝነስ ሞዴሎችን፣ ስልጠናን የ(ክህሎት የቢዝነስ ሞዴል ዝግጅት፣ የንግድ ሥራ አመራር) እና  ቁጥጥርን/ሬጉላቶሪ በማጠቃለል ቀጥተኛ መስመር ብቻ  ያልሆነና የተወሳሰበ የዕሴት ሰንሰለት ተዋንያቶች ያሉት ኢንጂነሪነግ የግብርና ሳይንስ አካል ነው፡፡ ይህ በኢንጂነሪነግ ሳይንስ ላይ የተመሰረተ  የግብርና መስክ በሚከተሉት ንዑስ የግብርና ዘርፎች ማለትም በእንስሳት፣ በእርሻ ልማት፣ በመስኖ ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የምርት የእሴት ሰንሰለታቸውን መሰረት አድርጎ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ይሰራል፡፡፣

የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በሥራ ላይ ለማዋል ክህሎትን ይጠይቃል በዚህ ሥራ ላይ መሰማራት የሚችለው የሰለጠነ የሰው ሃይል መሆኑ ከተለምዶው ግብርና ለየት ያደርገዋል፡፡ ይህን ዕድል እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የሰለጠነ የሰው ሃይል ግብርናውን እንዲቀላቀለና ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባቸዋል፡፡

ከብኢኮ ኢንደስትሪዎች አንዱ የሆነው አዳማ የእርሻ መሳሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የግብርና ሜካናይዜሽን የተቀላጠፈ እንዲሆን ለሚካናይዤሽን ስራ የሚያገለግሉ የተለያየ ሞዴልና የፈረስ ጉልበት ያላቸዉን ትራክተሮች፣ለመስኖ እርሻ የሚያገለግሉ የዉሃ ፓምፖችን፣ መከስከሻና ማረሻዎችን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚዉ መዘመን ጉልህ ድርሻ ያላቸዉ ምርቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡  ይህ ኢንዱስትሪ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች በቀጥታ አምርቶ ከማቅረቡም ባሻገር እነዚህ መሳሪያዎች የሚመረቱባቸው የማምረቻ ፋሲሊቲዎች እየገነባ ለግል ባለሀብቶች ያስተላልፋል፡፡

ኢንዱስትሪው በዘመነ ደርግ ሲቋቋም ሚካናይዜሽን እንዲስፋፋ  ታስቦ ነበር ፡፡ ኢንዱስትሪው የተቋቋመበትን ዓላማ እያሳካ ይሆን ? የግብርና ሚካናይዜሽን ሂደትና ደረጃ ምን ላይ ደርሷል? የሚካናይዜሽን ስራ እንዳይፋጠን ያደረጉት ማነቆዎች ምንድን ናቸው? ከአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ  ጊዜያዊ ስራ አስኪያጅ ከሻ/ቃ ድሪባ ሁንዴ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

 

#ብኢኮ፡-የግብርና ሚካናይዜሽን ሂደትና ደረጃ ምን ላይ ደርሷል?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡- መንግስት ሀገሪቷን ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር እያሸጋገረ ይገኛል፡፡ይህም  ግብርናውን ወደ ዘመናዊነት የማሸጋገር ሂደት ነው፡፡እስካሁን በሜካናይዜሽን ላይ የተሰራ ስራ የለም ፡፡  በመንግስትና በጥቂት አርሶ አደሮች ደረጃ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ብዙሃኑን አርሶ አደር ግን ያቀፈ  አይደለም፡፡ ሜቴክ ከተቋቋመ ጀምሮ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ሚካናይዜሽን እንዲስፋፋ ብዙ ሰርቷል ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ  ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

#ብኢኮ፡-የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ የግብርና ሚካናይዜሽን ላይ ምን እየሰራ ነው ?

#ሻ/ቃ  ድሪባ፡- የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ  እያንዳንዱ ክልል ሚካናይዜሽን ላይ እንዲሰራ በተለይም መካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኙ አርሶ አደር ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ለመካናይዜሽን ስራ የሚያገለግሉ የተለያየ አይነት ትራክተሮች፣ ፓምፖችንና ማሽኖችን እናቀርባለን ፡፡ ሽያጫቸውን በተመለከተ እታች ያለውን አርሶ አደር ያማከለ ነው፡፡ 50 በመቶ ከፍለው ቀሪውን በዱቤ ይወስዳሉ፡፡ኮላተራል አናስይዝም ፣ ወለድ  አናስከፍልም ይሄ እታች ያለውን ገንዘብ የሌለውን አርሶ አደር ያበረታታል ብለን እናምናለን፡፡መንግስትን በዚህ ደረጃ ሚካናይዜሽኑን ለመደገፍ ካልረዳነው በስተቀር ዘርፉን ማሳደግ አይቻልም፡፡

አሁን መንግስት በርሃ ለማልማት ትልቅ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሶማሌና አፋር ክልሎች  ፕሮጀክት ነበረን ፡፡ ከእሱ ወጥተናል ነገር ግን  ብዙ ትራክተሮች፣ ማረሻዎች፣መከስከሻዎች አሉን  እነዚህ ሚካናይዜሽኑን የሚደግፉ መሳሪያዎቸ  እያሉን በተጠቀሱት ክልሎች ያለ ስራ ይቀመጣል? በነዚህ ክልሎች በርሃ ማልማቱ ላይ  ሚካናይዜሽን ላይ መንግስት  ቢሰራ እንኳን ኢትዮጵያን ምስራቅ አፍሪካን መቀለብ የሚችል መሬት አለን፡፡ነገር ግን ሚካናይዜሽን ላይ አልተሰራም፡፡በአዳማ እርሻ መሳሪያዎች በኩል  በተቻለ መጠን ሁሉም ክልል  አርሶ አደሩ  ቴክኖሎጂውን እንዲያውቅ ለማስተዋወቅ ተሞክሯል ፡፡

#ብኢኮ፡-ዘርፉን ለማስተዋወቅ የሄዳችሁበት መንገድ ምን ይመስላል?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡-በራሳችን ወጪ  በተለያዩ ክልሎች  በመሄድ በነፃ አርሰን  በማሳየት የውሃ ፓምፖችን አጠቃቀም ፣  ኮምባይነር መጠቀም የማይችሉ ዝቅተኛ አርሶ አደሮች  በትናንሽ መውቂያዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አሳይተናል፡፡  በአማራ ፣ በኦሮሚያ ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ሚካናይዜሽንን በማስተዋወቅ ብዙ ስራ ሰርተናል፡፡ በተለይም በትግራይ ክልል አርሶ አደሩ ወደ ሚካናይዜሽን  እንዲገባ በነፃና አነስተኛ ገንዘብ በማስከፈል ብዙ ስራ ሰርተናል፡፡ለምሳሌ ከሁለት ሳምንት በፊት  አማራ ክልል በራሳችን ወጪ  ትራክተር ይዘን በመሄድ አርሶ አደሩ ወደ ሚካናይዜሽን እንዲገባ በተግባር አሳይተናል፡፡ምስራቅ ጎጃም በጣም ሰፊ መሬት አላቸው፡፡ ነገር ግን ትራክተር የላቸውም፡፡ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ መጠቀም ካልቻለ ሀገሪቷን ከግብርና  ወደ ኢንደስትሪ   በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሻገር አይቻልም፡፡ ኢንዱስትሪ እንዲኖር  የግብርና ግብዓቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡የግብርና ግብዓት በሌለበት ሁኔታ ኢንዱስትሪ ሊኖር አይችልም፡፡ስለዚህ መሰረታዊ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ ግብርናው ነው ፡፡ግብርናውን ሚካናይዝድ ማድረግ መንግስት ኩታ ገጠም የሚባሉ መሬቶች ላይ ጥሩ እየሰራ ነው እኛም ሚካናይዜሽኑን እየደገፍን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይቻላል፡፡በተቻለን መጠን ሁሉም ክልሎች ሚካናይዜሽን እንዲጠቀሙ እና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ሰርተናል፡፡

##ብኢኮ፡-ግብርናችን በሚካናይዜሽን ባለመደገፉ ምን አጋጠመው?

ሻ/ቃ ድሪባ፡- አሁን ከሁሉም ሀገሮች ትራክተር የማትጠቀም ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ካለን  ያልታረሰ መሬት አንፃር ትራክተር የለንም ማለት እንችላለን፡፡ ግብርናችን ስላልዘመነ ያለንን መሬት መጠቀም ስላልቻልን ሁሌም ስንዴ ከውጭ እንድናመጣ ሆነናል፡፡ ሚካናይዜሽን ቢሰራ አንደኛ የገበሬን ጉልበት ይቀንሳል፡፡ ማሽን ብንጠቀም ከውጭ የምናስገባውን እያንዳንዱን እህል ያስቀርልናል ፡፡ ሁለተኛ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት (inport)ምርት ወደ ውጭ ሀገር መላክ(Export) ላይ መስራት እንችላለን፡፡ለምሳሌ በብዛት ወደ ውጭ የምንልከው የግብርና ውጤቶችን ነው፡፡ ምርት ይኖራል ኢንዱስትሪውን አዘጋጅተን ፕሮሰስ አድርገን ወደ ውጭ መላክ እንችላለን፡፡ካልሆነ ደግሞ ሚካናይዝድ ካደረግን አርሶ አደሩንም ሆነ ማህበረሰቡን መቀለብ እንችላለን እንዲህ ማድረግ ስንችል ከውጭ የምናስገባው ስንዴ ይቀራል ማለት ነው፡፡

ሚካናይዜሽን ባለመጠቀማችን ተጎድተናል ለምሳሌ ዘይት ከውጭ ነው የምናስገባው፡፡ ሰሊጥ  የሚፈልገው ቆላማ የሆኑ ቦታዎችን ብናለማ በዘይት ምርት  ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡አማራ ፣ ትግራይና  ወለጋ አካባቢ የሰሊጥና የቡና  ምርት አለ ፡፡ አፋርና ሶማሌ ክልል ላይ መስራት ብንችል ከሀገራችን አልፈን ለሌላ መትረፍ እንችላለን፡፡ሱማሌና አፋር ቲማቲምና አታክልቶችን  ብናመርት  ለጅቡቲ  ኤክስፖርት ማድረግ እንችላለን፡፡ስለዚህ ሚካናይዝድ ያለማድረጋችን ቴክኖሎጂ ያለመጠቀማችን የእኛን ግብርና ከእጅ ወደ አፍ ብቻ አድርጎታል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ለማድረግም አልበቃንም በየዓመቱ እርዳታ እየጠየቅን ወይንም መንግስት ገዝቶ  እየረዳን ነው ስለዚህ ግብርናችን ሚካናይዝድ ባለመደረጉ በጣም ትልቅ ጉዳት አለው የሚል እሳቤ አለኝ፡፡

#ብኢኮ ፡-በሀገራችን የግብርና ሚካናይዜሽን እንዳይስፋፋ ማነቆ የሆኑበት  ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

#ሻ/ቃ ድሪባ ፡- በሀገራችን የግብርና ሚካናይዜሽን እንዳይስፋፋ ማነቆ ከሆኑበት  ምክንያቶች የመጀመሪያው የግብርና ሚካናይዜሽን ድጋፍ የለውም ፡፡ አርሶ አደሩ ላይ ትኩረት ተደርጎ አልተሰራም፡፡ ሌላው ደግሞ ቴክኖሎጂ ላይ አልተሰራም፡፡ ለእያንዳንዱ ነገር መሰረቱ ግብርና መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል፡፡በእኔ አመለካከት አርሶ አደር ላይ ወይም እርሻ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰራ ስራ የለም ፡፡ በሁለተኛነት መንግስት እጁን አስገብቶ ካልረዳው በስተቀር አርሶ አደሩ አቅም የለውም  ፡፡ ወደ ግብርና ትኩረት ተደርጎ ካላተሰራ  አርሶ አደሩ ያለችው መሬት ትንሽ  ናት ትራክተርና ኮምባይነር ለመግዛት አቅም የለውም፡፡ የተማረውን ህብረተሰብ ወደ ግብርና በመውሰድ ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀም ማስተማር ከትንሹ ጀምሮ ቀስ በቀስ ማስጀመር ያስፈልጋል፡፡በትልቅ ደረጃ  ግብርናን ከተወሰኑ ሰዎች ውጪ ኢንቨስተሮችም የሚመርጠው የለም፡፡ባለ ሀብቱም ከተማ ላይ ተንጠልጥሎ ፋብሪካ ማቋቋም እንጂ ግብርናውን አይፈልገውም፡፡የምርት ግብአቱንም ለመውሰድ ኢንፖርት ኤክስፖርት ለማድረግ አይፈልግም፡፡ ግብርና የሚሰጠው ጥቅም ስላልተለመደ ወደ ታች ተወርዶ አልተሰራበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

#ብኢኮ፡- ከክልሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

#ሻ/ቃ  ድሪባ ፡-ከክልሎች ጋር በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ሚካናይዜሽን እንዲለመድ ጥሩ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ከደቡብ፣ከሶማሌ፣ከአፋር ክልሎች ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አለን፡፡ እራሳችንም እየሄድን ተወካዮቻችንን አስገብተን ጥሩ የሚባል ግንኙነት መስርተናል፡፡ ከአማራና ከትግራይ ክልል ጋር ቀደም ሲል ከተከፋፈሉት መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ነበር ፡፡ የነበሩ ሀላፊዎች እታች ድረስ ወርደው ያለመስራት ችግር ነበረ፡፡ በ2013 ዓ.ም ከሁሉም ክልሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እየሰራን ነው ፡፡

#ብኢኮ ፡-ለሚካናይዤሽን ስራ የሚያገለግሉ ምርቶች አቅርቦታችሁ ምን ይመስላል?መለዋወጫስ?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡- በብዛት በዱቤ ስለምንሸጥ ብዙ ክምችት አለን ፡፡በተለይም ትራክተር ፡፡ፓምፖችም ከበቂ በላይ አሉን ፡፡ በዚህ ዓመት የተጠየቅነውን በሙሉ ምላሽ ሰጥተናል፡፡ትራክተሮችን ፓምፖቹም ላይ ውል አስረን ሽያጭ ፈፅመናል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅርብ  ወደ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ፓምፖችን ውል አስረን እያስረከብን ነው፡፡ከአዲስ አበባ መስተዳድር ከተማ ማልማት ጋር ፓምፕና ትራክተሮች ሽጠንላቸዋል ከአርሶ አደሮች ውጪ ማለት ነው ፡፡ ትራክተር በቁጥር ስለሚጠይቁን  በግለሰብ ደረጃ ከሁሉም ጋራ ውል አስረን አስረክበን ጨርሰናል ፡፡በኢንዱስትሪያችን ብዙ ክምችት ስላለን በዚህ በጣም ስኬታማ ነን፡፡

የመለዋወጫ አቅርቦት ከሞላ ጎደል እያቀረብን ነው ፡፡ ነገር ግን አሁንም ክፍተት አለ ፡፡በቀጣዩ አመት ትልቁ ትኩረታችን መለዋወጫ ላይ መስራት ነው ፡፡ያሉትንም ትራክተሮች ብራንድ ቀይረን አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የተሻሉ ብራንዶችን   እስከ መለዋወጫቸው ለማቅረብ አስበናል፡፡አሁን በቅርበት  መስራት ያሰብነው  ብዙ ትራክተሮች የተሸጡበት ክልል ላይ  የተወሰኑ ጋረዦችን እያቋቋምን የትምህርት ዝግጅቱ ያላቸውን ስራ አጥ ወጣቶችን በማሰልጠን  እንዲሰሩ መለዋወጫም አዘጋጅተን ለ2013 ዝግጁ እናደርጋለን፡፡

#ብኢኮ ፡-ግብርና ሚካናይዜሽንን በተመለከተ የምትሠጡት ስልጠና ካለ?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡-በሁሉም ምርቶች ሁለት አይነት ስልጠና እንሰጣለን፡፡ የመጀመሪያው በኢንዱስትሪ ደረጃ በደንበኛ ፍላጎት በመረጠው ቦታ እንሰጣለን፡፡ በየትኛውም ቦታ በየትኛውም ክልል ላይ፡፡ ለምሳሌ ትራክተር ለሚገዛን በኛ ጊቤ ውስጥ  ስልጠና እንሰጠዋለን ፡፡ እርሻ ላይ በደንብ እሰለጥናለሁ ካለ ቦታው ድረስ ሄደን አሰልጥነን ሰርተፊኬት ሰጥተነው እንመለሳለን፡፡

#ብኢኮ፡-ባለንበት የመኸር ወቅት ገበያችሁ ምን ይመስላል?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡-ዘንድሮ ሽያጭ ላይ በተለያየ ምክንያት ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡በተለይ  በሚያዝያ፣ በግንቦትና በሰኔ  ትላልቅ ትራክተሮች የሚሸጡበት በጣም ከፍተኛ ሽያጭ የሚኖርበት ወቅት ነበር  ከሌላ ወቅት አንፃር ስናየው በኮሮናና በሌሎች ምክንያቶች ሽያጫችን ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡ በፓምፕ ደረጃ ግን ጥሩ ሽያጭ አለን ክልሎቹ ፓምፖቹን በደንብ ስላዩት በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ መስተዳድር ፣ውሃና መስኖ ኢነርጂ፣ኦሮሚያ ክልል፣አማራ ክልል እነዚህን ፓምፖች  እየጠየቁን ስለሆነ ስርጭት ላይ  ጥሩ ነው፡፡

#ብኢኮ ፡-ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡- ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ያሉንን ምርቶች እናስታውቃቸዋለን፡፡እነሱ በሚያቀርቡት ስብሰባ ላይ እየተሳተፍን  ፍላጎታቸውን እንረዳለን፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ምን ይፈልጋል? በ2013 ምን አቀደ? ምን ለመስራት አስቧል? የሚለውን የእነሱንም ፍላጉት እንጠይቃለን፡፡ በቅርብ ጊዜም የብኢኮ ዋና ዳይሬክተር ባመቻቹልን መሰረት  እኛ ጋር ያሉትን እቃዎች ዝርዝር ለክቡር ሚኒስትሩ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አቅርበናል፡፡ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ፣ከውሃ ሀብት ቢሮ፣ ከግብርና ሚኒስቴር ፣ ከኢነርጂና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከነዚህ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር በተቻለ መጠን በቅርበት ከድሮው በተሻለ አብረን እየሰራን እንገኛለን፡፡

#ብኢኮ ፡-የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

#ሻ/ቃ ድሪባ፡-አዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ ከተቋቋመ በጣም እረዥም ዓመት ነው፡፡ ግብርና ስራ ላይ በጣም ልምድ አለው፡፡ በተለይ የግብርና እርሻ መሳሪያዎች ላይ ፡፡ሲቋቋም ለሚካናይዜሽን ስራ ተብሎ ነው፡፡በደርግ ዘመን ሚካናይዜሽን እንዲስፋፋ ታስቦ  የተቋቋመ ነው፡፡ መንግስት ግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ በብዙ አጋጣሚ ሁሉንም ክልሎች የማየት አጋጣሚ ነበረኝ እኔ እንደተመለከትኩት የኢትዮጵያ መሬት ምንም አልተነካም በተለይም አፋርና  ሱማሌ ክልል ኢትዮጵያን መቀለብ የሚችል መሬት ያላቸው ክልሎች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በፕሮጀክቱ ላይ ሜቴክም የመሳተፍ እድሉን አግኝቶ ነበር ብዙ የውሃ ጉድጓዶች ወጥተው በእራሳቸው ጊዜ የሚፈሱ መሬት ያጡ እነዚህን መሬቶች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይህንን ፕሮጀክት ወደ ስራ ቢያስገባ ደስ ይለኛል፡፡ኢትዮጵያ መጀመሪያ የምትቀየረው ግብርና ስትቀይር ነው፡፡ግብርናው ካልተቀየረ ምንም ነገር መቀየር አይቻልም ኢንዱስትሪም አይመጣም ፡፡ የኢንዱስትሪ ግብዓትም አይኖርም፡፡ ትልቁ ነገር መንግስት አሁን የጀመረው በረሃን ማልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራ እንኳንም ለእኛ ለምስራቅ አፍሪካም እንተርፋለን የሚል እምነት አለኝ::

#ብኢኮ፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

 #ብኢኮ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡