ብኢኮ አርአያ ተቋም ተብሎ ተሸለመ

ብኢኮ አርአያ ተቋም ተብሎ ተሸለመ

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የአርአያ ሴቶችና አርአያ ተቋማት የሽልማት እና ዕውቅና አሠጣጥ ስነ-ስርዓት ብኢኮ በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አርአያ ተቋም በመሆን ተሸልሟል፡፡

የሽልማትና እውቀት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዮሃንስ ዲንቃዮህ ብኢኮ በሀገራችን የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴዎችና በመከላከያ ስራዊቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዘርፍ ላይ እያደገው ከሚገኝ አስተዋፅኦ ባሻገር በተቋሙ ሁሉን አቀፍ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረጉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡

            የዕውቅና ሽልማቱን ከሚኒስትር  ዲኤታው እጅ የተቀበሉት የብኢኮ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው በኮርፖሬሽኑ የተሻለ ተሳትፎና ተጠቃሚነት  የብኢኮ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለዳይሬክቶሬቱ ኃላፊ እና አጠቃላይ መዋቅር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

            ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሽልማቱ ተቋማቸውን ለበለጠ ስራ እና ውጤት እንደሚያነሳሳው ጠቅሰው አስከ አሁን የተገኙ ውጤቶች ተጠብቀው እንደሚሄዱ አረጋግጠዋል፡፡

ብኢኮ ካሉት ከ19ሺህ በላይ ሰራተኞች ከ6500 በላይ ሴት ሰራተኞች እንዳሉትና ከእነዚህም    ሴቶች በአመራርና ውሳኔ ሰጪነት የሚገኙ መሆናቸውን በእለቱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተምሳሌነት በሚያስጠቅስ መንገድ በተቋሙ ውስጥ ላሉት ሰራተኞች አገልግሎት የሚሰጡ አምስት የህፃናት ማዋያ ማዕከላት በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉንና እስከ 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ አስር የህፃናት መዋያ ማዕከላትና ትምህርት ቤቶች ለመክፈት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዕለቱ በመከላከያ ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አርአያ አንእስት ተብለው ከተሸለሙ አምስት ሴቶች በብኢኮ የተገኘውን ስኬት እንዲመጣ ብቁ አመራር የሰጡት የብኢኮ ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሲሳይ ገ/መስቀል ናቸው፡፡