ኦሞ አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በመጨረሻው ምዕራፍ

ኦሞ አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በመጨረሻው ምዕራፍ

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ ከሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶች አንድ የሆነው ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጄክት ግንባታው ተጠናቅቆ የምርት ሙከራውን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

ዋና ዋናዎቹ የፕሮጀክቱ የግንባታ ስራዎች መጠናቀቃቸውን የገለፁት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ሌ/ኮ ዮሃንስ ትኬሳ በአሁኑ ሰዓት የፋብሪካው ልዩ ልዩ አካላት እርስ በርሳቸው የማናበብና የተተከሉ ማሽኖች በትክክል ስለመስራታቸው የማረጋገጥና ስራውም እየተገባደደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ ሰራተኞች በማሳተፍ እየተገነባ ያለው ኦሞ አንድ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተገነባ በመሆኑ በገንዘብ የማይታመን የእውቀትና ቴክኖሎጂ አቅም መፍጠሩን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡

የፋብካሪካው መገንባት ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የተፈጠሩ የስራ ዕድሎች የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በማዘመን ላይ እንደሚገኙ የአካባቢው ኗሪዎች ይናገራሉ፡፡

የሙርሲ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው ወጣት ሞሮኮ በአርብቶ አደርነት ከሚተዳደር ቤተሰብ የተገኘ አርብቶ አደር ነበር፡፡ ወጣቱ በብኢኮ የተመቻቸለትን ስልጠና ወስዶ በሜታል ፋብሪኬሽን ሙያ ለፕሮጀክቱ ተቀጥሮ ይሰራል፡፡ ወጣት ሞሮኮ በአሁኑ ሰዓት ኑሮው መሻሻሉንና ለወደፊት በሙያው ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ እያለመ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡